TPLF cannot be reformed. Like apartheid, it should be dismantled! - ETHIOMEDIA

ያልተፈታው አራተኛ መንግስት እና የዶ/ር አብይ ዝምታ! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

“በኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲረጋገጥ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የዘለቀ… ደም አፋሳሽ እና እልህ አስጨራሽ የታሪክ ሂደት ውስጥ አልፈናል። የዚህ ሁሉ መነሻ ምክንያት ደግሞ፤ አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የኢህአዴግ ፖለቲካ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት ቀደም ሲል የፈጸማቸውን ስህተቶች በማመን፤ በተለያዩ ግዜያት ህዝቡን ይቅርታ ጠይቋል። ሆኖም ከነጻ-ፕሬስ ጋር በተያያዘ ታስረው የተፈቱትንም፤ ወድቀው የተነሱትን ጋዜጠኞች ይቅርታ ማለት ቀርቶ፤ ነጻ-ፕሬስ ዳግም በኢትዮጵያ እንዲያብብ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያደርግ አልተመለከትንም።” ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ከጻፍነው ደብዳቤ ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ።

ዳዊት ከበደ ወየሳ (EMF) የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ፤ እውነትን ስለመሰከሩ፤ ብዙዎቹ ታስረው ተፈተዋል። ሌሎች ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል። የተቀሩት ደግሞ ይህንን ቀን ለማየት እንኳን እድሉን ሳያገኙ አልፈዋል። ይህ ሁሉ የሆነው… ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲረጋገጥ ለማድረግ በሚደረገው ግብግብ መሃል ነው። ዛሬ የተሰዉ ጓዶቻችንን እናስባቸዋለን፤ የተሰደድነውም እንመለሳለን፤ የታሰሩትም ተፈትተዋል። እኛ ከታሪክ ወቀሳም ጭምር ነጻ ነን። ጋዜጠኞቻችንም ከእስር ተፈትተው ነጻ ናቸው። እነሆ የተሰደድንበት፣ የሞትንለት እና የታሰርንለት “ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነት” ገና አልተፈታም – እንደታሰረ ነው።

Image result for ethiopian free press journalists association

ይህ ነጻነት የታሰረው ደግሞ በህግ ነው። በቅድሚያ በ1985 የታወጀው የፕሬስ ነጻነት፤ በ1996 በህግ እንዲፈርስ ተደረገ። ከዚያም የፕሬሱን አባላት እንደጠላት እያሳደዱ በወንጀል እና በአገር ክህደት መክሰስ ተለመደ። ለዚህ ሰይጣናዊ ስራ በረከት ስምኦን እና ሽመልስ ከማል ግንባር ቀደም ሆነው ተሰለፉ። ከጀርባቸውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊ አቃቤ ህጋውያን እና የፖሊስ ኃይላት፤ እንዲሁም የደህንነት አባላት ተኮለኮሉ። በዚህ አይነት እነበረከት ስምኦን ያደራጁት መቺ ኃይል ፕሬሱንና አባላቱን አናት አናቱን እየመቱ ምንጩን ለማድረቅ ብዙ በጣም ብዙ ሰሩ።

እነዚህ ሰዎች ከድፍረታቸው ብዛት የተነሳ… ኢትዮጵያዊነትን ስለሰበክን በዘር ማጥፋት ወንጀል ጭምር ከሰሱን። ይህ አልበቃ ብሎ… አሸባሪዎችን ለመቆጣጠር በሚል ሽፋን የሽብር ህግ አውጥተው፤ የቀን ጅቦችን ያጋልጡ የነበሩ ጋዜጠኞችን “አሸባሪዎች” ብለው በአሸባሪነት የሚከሱበትና የሚያስሩበት አምባገነናዊ ስርአት አቋቋሙ። እነዚህ አሳሪ እና አናቂ የሆኑ ህጎች አሁንም አልተሰረዙም። እነዚህ ህጎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ህጉን ያረቀቁት እነሽመልስ ከማል እና በረከት ስምኦን፤ ህጉ ሲወጣ በጭብጨባ ያጸደቁት የፓርላማ አባላትና ህጉን ሲያስፈጽሙ የነበሩ ነጭ ለባሾች ዛሬም ድረስ  አሉ። ዛሬ ከውጥ መጥቷል ተብሎ ላይ ላዩን ይጨፈራል እንጂ፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ግን ገና ነጻ አልወጣም።

በሚዲያ ላይ የሚደረገው አፈና ምክንያት ከ162 በላይ ጋዜጠኞች ለስደት ሲዳረጉ፤ የመሰደዳቸው ዋና ምክንያት በመንግስት በኩል የተቋቋመው መቺ ቡድን ነው። ይህ የአምባገነኖችን በትር ይዞ ከፊት እየመራ መንገድ ሲጠርግ የነበረ አካል፤ እንደቀበሮ ባህታዊ ለምድ ለብሶ በየመዋቅሩ ውስጥ እንዳደፈጠ… አሁንም ህያው ሆኖ አለ። በዚህም ምክንያት ሊሆን ይችላል… ስለነጻ-ሚዲያ እና ስለጋዜጠኛው ነጻነት የሚሟገት ተቋም በፋኖስ ፈልገን ማግኘት አልቻልንም። ትላንት በዚያ ጨለማ ዘመን የህዝቡን ድምጽ ሲያሰሙ የነበሩ ጋዜጠኞች ተዘንግተው፤ ለዛሬው ድል ሌሎች ሲሞካሹበትና ሲወደሱበት እያየን… “የበሬን ውለታ…” ማለታችን አልቀረም።

“የበሬን ውለታ፣ ወሰደው ፈረሱ፤

ከኋላ ተነስቶ፣ ቀድሞ በመድረሱ።”

ይህም ሁሉ ሆኖ ደግሞ ሌላ የሚገርም ነገር እናውጋቹህ። “የምህረት እና የይቅርታ አዋጅ” የሚባል ነገር አለ። ይህ አዋጅ ምህረት የሚሰጠው በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የተለዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦችን ነው። የነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞችን የሚያካትት አይደለም። ቢያካትትም እንኳን፤ እኛው በደል ደርሶብን… እኛው ሞተን እና ተሰደን፤ ተሰቃይተን እና ታስረን… በዳይ ይቅርታ ሊለን ሲገባ፤  ከበዳያችን ጉልበት ስር ተንበርክከን “ምህረትህን አውርድልን፤ ይቅርታህንም ስጠን!” እንድንል ይፈለጋል። ይህ ሊሆን አይችልም… እንደሰነፍ ቆሎ ልትቆረጭሙንማ አይቻልም። በህግ አምላክ ጎበዝ! ቁጭ ብለን ልንነጋር ይገባል።

ይህንንም ይሁን ብለን ብናልፍ እንኳን፤ የተባለው የምህረት አዋጅ የማይመለከተን ሰዎች አለን። ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ በራሳችን የደሰውን እንደምሳሌ በመጥቀስ ጥቂት እንጨዋወት። ቀደም ባለው ዘመን አብዛኛው ጋዜጠኛ “ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት፤ ህዝብን በመንግስት ላይ ለማሳመጽ” በሚሉና ህገ መንግስቱን ለማፍረስ… በኋላም ላይ በአገር ክህደት እና በዘር ማጥፋት ወንጀል የተከሰስን፤ ተከሰንም እድሜ ልክ እና ሞት የተፈረደብን ጋዜጠኞች አለን።

ከጥቂት ወራት በፊት በውጭ የምንገኝ ጋዜጠኞች ዳላስ ቴክሳስ ላይ ስብሰባ ባደረግንበት ወቅት፤ እዚያ ከተገኙት ሰዎች መካከል የአሜሪካው ድምጽ ጋዜጠኛ አዲሱ አበበ አንደኛው ነበር። ከ1997ቱ ሁከት በኋላ በጅምላ ስንከሰስ፤ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ክፍለ ግዜ ይሰሩ የነበሩ አራት ጋዜጠኞች በአገር ክህደት እና በዘር ማጥፋት ወንጀል መከሰሳቸው ይታወሳል። እናም የነሱን ጉዳይ አንስተን መጨዋወታችን አልቀረም። “የሆነስ ሆነና የናንተ ጉዳይ እንዴት ሆነ?” ስንል፤ በወቅቱ “ክሱ ተቋርጧል!” ከመባሉ ውጪ ምንም እንደማያውቁ ነው ያሳወቀን። እንግዲህ ይህ ማለት በተንኮለኞች የህግ ትንታኔ ስናየው፤ “በነሱ ላይ የተመሰረተው ክስ ለግዜው ተቋረጠ እንጂ አልተነሳላቸውም!” የሚል ትርጓሜ ይዞ እናገኘዋለን።

ሌላው ጋዜጠኛ ጓደኛችን አክሊሉ ታደሰ ነው፤ “የሰላማዊ ትግሉ አብቅቶለታል! ብሎ በማመኑ ግንቦት ሰባትን ተቀላቅሎ ሰርቷል። በዚህ ምክንያት በሌለበት የሞት ፍርድ ተበይኖበታል። በአዋጁ መሰረት ይህ ብይን ሊነሳለት ይችል ይሆናል ብለን እናስብ። ነገር ግን ድሮ ተከሶበት ፍርድ ያልተሰጠበት፤ የሰሜን ሸዋ አርበኞች ጉዳይ ተነስቶ፤ አሮጌ ፋይል ተከፍቶ “በላ ልበልሃ!” ሊባልልን ይችል ይሆን ይሆናል።

ዘላለም ገብሬ በጋዜጠኝነት ሲሰራ ቆይቶ በ97ቱ ምርጫ ወቅት፤ ፎቶው ጭምር በቴሌቪዥን እየታየ ሲፈለግ፤ አገር ለቆ ወጥቶ ኬንያ ገባ። ወደ አሜሪካ ከመሻገሩ በፊት በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከሶ፤ በሌለበት እድሜ ልክ ተፈርዶበታል። (ያው የሞት ፍርድ እንደማለት ነው)  እንዲህ እንዲህ እያልን የብዙ ጋዜጠኞችን ጉዳይ ብንዘረዝር፤ ነጻነታቸው ያለው ይህ ግርግር እስከሚያልፍ እንጂ፤ ዘላቂ የሆነ መተማመኛ እንዳላገኙ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በዚያ ላይ የምህረት አዋጁ ደግሞ በዘር ማጥፋት የተከሰሱትን ሰዎች አይመለከትም። እናም ስማቸው በወርቅ ቀለም ከመጻፍ ይልቅ፤ በዘር ማጥፋት ተከሰው  እንደነኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ስማቸው በጥቁር መዝገብ ላይ የተከተቡ መኖራቸውን ስንነግርዎ… “የጉድ አገር” ብለው ዝም እንዲሉ አንፈልግም።

በአጭር አነጋገር የምህረት አዋጁ ሁሉንም ጋዜጠኛ ነጻ አያወጣም። በዘር ማጥፋት የተከሰስነው ሞት ሊጠብቀን፤ በአገር ክህደት የተፈረጅነውም፤ ጉዳያችን በወታደራዊ ፍርድ ቤት ይታይ ይሆን ይሆናል። ስለዚህ አዋጁን ተከትለን አገር ቤት ብንገባ፤ በዘር ማጥፋትም ሆነ በሌሎች ወንጀሎች የተከሰስን ሰዎች፤ የድሮው ክስ ፋይላችንም ገና አልተዘጋምና “ያንተ ጉዳይማ በወንጀለኛ መቅጫው መሰረት የተያዘ ስለሆነ ነጻ አይደለህም” የሚል አካል ቢመጣ፤ ምንም መከላከያ የለንም።

ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ) በህገ ወጥ መንገድ ከአባላቱ ተወስዷል። የማህበሩም ፕሬዘዳንት አቶ ክፍሌ ሙላት እና ሌሎች አመራሮች ለስደት ተዳርገዋል። ይህ ሁሉ ክፍተት የተፈጠረው በጋዜጠኛው እና በማህበሩ ላይ ሆን ተብሎ በተፈጠረ ጫና ነው። ከዚህ በኋላ ሁኔታዎችን ወደነበሩበት መመለስ የሚቻለው፤ የታሰረውን ነጻነት እና የታፈነውን ማህበር ነጻ ማውጣት ስንችል ብቻ ይሆናል።

ስለዚህ ደጋግመው… “በምህረት አዋጁ ነጻ ሆናችኋል” የሚሉን ሰዎች፤ አንድ አፍታ ቆም ብለው፤ ጉዳዩን በኛ ቦታ ሆነው እንዲያዩልን እንሻለን።  ስለሆነም በህይወት ያለነውን ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው ያለፈ ጓደኞቻችንንም መልካም ስም ጭምር ነጻ የሚያወጣ አስተማማኝ ነጻነት ሊኖር ይገባል። በዚህ መሰረት በዝርዝር የምናውቃቸው 162ቱም ጋዜጠኞች፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከፍቶባቸው የነበረው የክስ ፋይል ተዘግቶ ነጻ ስለመሆናቸው ዋስትና ማግኘት ይኖርብናል።

መግቢያችንን ያደረግነው… ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከተጻፈው ደብዳቤ ላይ ቀንጨብ አድርገውን በመውሰድ ነው። አሁን ደግሞ ለሚንስትሮች ምክር ቤት እና ለህግ አካላት እንዲደርስ ካደረግነው ደብዳቤ፤ የመጨረሻዎቹን አንቀጾች እዚህ ላይ በመጠቀም እንሰነባበት።

በአለም አቀፍ ጋዜጠኞች ማህበር እና በእኛ በኩል ቢያንስ ከ162 በላይ ጋዜጠኞች በዝርዝር አለን። እንደእውነቱ ከሆነ በ’ነዚህ ጋዜጠኞች ላይ የተከፈተባቸው የወንጀል ክስ፤ ሆን ተብሎ ግለሰቦቹን ለመጉዳት ብሎም አማራጭ በማጣት አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ የተደረገ እንጂ፤ በአገር ክህደት እና በዘር ማጥፋት ወይም በሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች ሊከሰሱ ባልተገባ ነበር። አልፎ ተርፎም ለጋዜጠኞች መብት ይቆም የነበረው ህጋዊ ማህበር በትዕዛዝ እንዲፈርስ መደረጉ በምንም መመዘኛ አግባብ አለመሆኑን የፍርድ ቤት ፋይሎችን በመመልከት ብቻ፤ የህሊና ፍርድ መስጠት ይቻላል።

የ’ነዚህን በስደት የሚገኙ ጋዜጠኞች ጉዳይ አስመልክቶ፤ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት  በጉዳዩ ላይ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፤ ብዙዎቹ ዝምታን በመምረጣቸው፤ በጋዜጠኞቹ ላይ ያላግባብ የተወሰነው ውሳኔ ትክክል እንደሆነ ተደርጎ ተወስዷል። ይህ መንግስት እና ይህ ዘመን አላፊ ነው። ትውልድ ግን አያልፍም። በነዚህ ጋዜጠኞች ላይ ያላግባብ የተወሰደባቸው እርምጃ እና ውሳኔም ካሁኑ እልባት ካላገኘ… በዘመናቸውም ሆነ በመጪው ትውልድ ጭምር፤ በልጆቻቸውና በወገኖቻቸው እንደወንጀለኛ መቆጠራቸው ትክክል አይደለም።

በመሆኑም እንዲህ ያለውን ክስ የመሰረዝ ሙሉ ስልጣን ያለው የሚንስትሮች ምክር ቤት፤ በውጭ አገር የሚገኙ የቀድሞች ጋዜጠኞችን ጉዳይ በጥሞና ተመልክቶ በጠቅላይ አቃቤ ህጉ በኩል፤ በሁሉም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ተመስርቶብን የነበረው ክስ እንዲሰረዝ እና እንዲነሳልን በማክበር እንጠይቃለን።

(Visited 11 times, 1 visits today)

You might be interested in