TPLF cannot be reformed. Like apartheid, it should be dismantled! - ETHIOMEDIA

ዶክተር ዐቢይ! ባልደግፍህ እንኳን እንቃፋት ላልሆንብህ ቃል በምድር፣ ቃል በሰማይ እገባልሀለሁ!

(ከወንድሙ መኰንን |ኢንግላንድ| 08/11/2018) – ገና ወያኔ ሥልጣን እንደያዘና፣ ምድረ ዘረኛ ሁሉ ተነስቶ ኢትዮጵያን እንደታረደ ድልብ በሬ ቅርጫ ተቀራምቶ የራሱን ትናንሽ መንግሥት ፈጥሮ ሊያጠፋት ሲሯሯጥ፣ የኢትዮጵያን ስም ጠባብ ጎሰኛ በወያኔ መሪነት፣ እያጎደፈ ሲዘልፋት፣ ለነጻነቷ ተዋግተው የወደቁላትን አርበኞቻችንን ሲሳለቅባቸው፣ በስድ ንባብ ጽፌ የልቤን ማድርስ ሲያቅተኝ፣ በተጎላደፈ እንግሊዝኛ ግጥም መጻፍ ጀመርኩ። እንደአጋጣሚ ሁኖ ግጥሞቹ ከኢ-ሜል (ያን ጊዜ ብርቅዬ ነበር) ስርጭትም አልፎ በኢትዮጵያን ሪቪውና በኢትዮጵያን ረጂስተር ምጽሔቶች ላይ ይታተሙልኝ ገቡ። ሰዎች የኔን የተጎላደፈ እንግሊዝኛ ግጥሞ እያነበቡ ያደንቁልኝ ጀመር። በተለይ “Son of a Neftegna” (አገር ጠባቂ ዘበኛ) እና “The Priceless Treasure” (ወደርየለሽ) የሚባሉ ግጥሞቼ በተማረው ሕብረተሰብ ዘንድ በብዛት ተሰራጩልኝ። ታዲያ የሚቀርቡኝ ጓደኞቼ፣ ዕውነተኛ ጸሐፊ መስዬአቸው “ምነው እንደዚህ የምትጽፍ ከሆነ፣ ምናለበት በአማርኛ ብትጽፍና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እጅ ገብቶ ቢነበብልህ” ብለው መጠየቅ ጀመሩ። መልሴ አጭር ነበር። “ከኔ ሽህ ጊዜ የሚማርኩ፣ ባማረ አማርኛ ተነበው የማይጠገቡ የአማርኛ ግጥም ጸሐፊዎች በምድሪቱ ስለሞሉ፣ የኔን ቅርቅንቦ ምንም ስሜት የማይሰጡ የአማርኛ ግጥብጥብ ግጥሞቼን ማን ያነብልኛል? በእንግሊዝኛ ግጥም የሚገጥሙ ኢትዮጵያውያን በጣት የሚቆጠሩ ስለሆኑ፣ እኔ የአማርኛውን የግጥም አጻጻፍ ሕግ ተከትዬ፣ በእንግሊዝኛ ስጽፍ ገቢያዬ የቱ ጋ እንዳለ የማውቅ እኔ ነኝ” እያልኩ በሳቅ እሸኛቸው ነበር።<

ዛሬም ጓደኞቼ በኢ-ሜልና በቴክስት አንድ የሚጠይቁኝ ጥያቄ አለ። እሱም “ምነው ለታሰሩት፣ ለተገደሉት፣ ለተሰደዱት የረሀብ አድማ ሳይቀር እያደረግክ፣ ስትጽፍላቸው፣ ስትጮህላቸው ኑረህ፣ አሁን ያ ሁሉ ጥረት ተሳክቶ፣ በመጨረሻ፣ አንተ “ወያኔ ከላይ የደረባቸው የማታለያ ካባ” እያልክ ስታላግጥባቸው፣ አንድ ቀን እንኳን ወያኔ እንጂ ኢሕአዴግ ያላልካቸው ኢሕአዴጎች ነቅተው ከወያኔ ጉያ እራሳቸውን ፈልቅቀው በማውጣት ለኢትዮጵያ አንድነት የሚቆሙ እንደነዐቢይ፣ ለማ፣ ገዱና ደመቀ ያሉ በሕይወታቸው የቆረጡ የኢትዮጵያ ጠበቆች በቄሮ፣ በፋኖ፣ በዘርማ፣ በነበሮ እየተደገፉ ሲወጡ፣ ምነው ትናጋህ ተዘጋ?” ብለው ይወተውቱኛል። መልሴ አሁንም አጭር ነው። 24 ሰዓት ሙሉ ጊዜያቸውን ሰውተው የዶር ዐቢይንና የለማን ቡድን (ቲም) ለነ ደመቀንና ለገዱን ሥራ መሳካት ከኔ በሺህ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ የድጋፍ ድምጻቸውን የሚሰጡ ማሕበራዊ ሜዲያውን ስለሞሉት፣ እኔ ድምጽ ባሰማ ባላሰማ ሚዛን አይደፋም። ስለዚህ ዝም ብዬ ከዳር ቁመ ማየቱ ለኔ ትልቅ ዕረፍት ነው በማለት እመልሳለሁ።

ስለእነ ዶክተር ዐቢይ ምን አስተያየት አለህ ለሚሉኝ፣ የግል አስተያየቴ ገና ሲጀመር “QUE SERA SERA” (እናያለን ለማለት)፣ የሶቪይት ሕብረትን ኮሙኒስት ፓርቲንና (ጋርባቾቭ) እና የደቡብ አፍሪካን አፓርታይድ (ዲ ክለርክ) ተመክሮ በማውሳት አንጻራዊ ድጋፌን እንደማንኛውም አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይችላል በማለት ሀሳቤን ሰጥቼአለሁ። አልፎ አልፎም ይኸ ጥሩ ነው (የእስረኞቹ መፈታት)፣ ይኸ ጥሩ አይደለም (የኢትዮጵያ አየር መንገደ ለመሸጥ መንሳት) በማለት ድምጼ ባይሰማም አስተያየቴን ወረውሬአለሁ። አባቶች፣ “ያለውን የወረወረ ፈሪ አይባልም” ይሉ የለ? ከግንባር አልቅደም እንጂ፣ ከሚደግፉት መሀል ነኝ። ግን፣ የኔ ድምጽ አሁንም የሚሰማው፣ ለታሠሩት፣ ለተገደሉት፣ ለተፈናቀሉት፣ ለተሰደዱት ስጮህ እንጂ፣ ያንን ለመደገፍ ወይም ይኸን ለመንቀፍ (ወያኔን አይጨምርም) አያምርብኝም። ለድጋፉ ከኔ የበለጡ ጓደምቼና የቤተሰብ አባሎቼ፣ እንደነ ዶር ቢሪ ያያ፣ ጸጋ መንክር እና የመሳስለሉት፣ ደከመን፣ ሰለቸን ሳይሉ 24 ሰዓት፣ 7 ቀናት፣ ከወር እስከወር የሚሠሩ ሞልተውላቸውል። ልክ እንደአማርኛው ግጥሜ የኔ አይጥሜ ነው ለማለት ነው።

ዶክተር ዓቢይና የለማ ቡድን፣ ገዱና ደመቀም ተጨምሮባቸው በሚከተሉት ነገሮች በግሌ አስደስተውኛል።

  1. ወያኔ ሙታ ተሟሙታ አገሪቱን ወደ እስር ቤት ቀይራ ሁሉንም ታሳሪ ያደረገቺውን ወህኒ ቤት በርግደው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩትን እስረኞችን ፈተውልናል። በተለይ የአንዳርጋቸው ጽጌ፣ ከእሥራት መፈታት ለኔ ትልቅ ትርጉም አለው። ከጋዜተኞቹ እነእስክንደር ነጋና ከፖሊቲከኞች ዕድሜ ልክ እሥራትና የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው እነ አንዱዓለም አራጌ የመሳሰሉት መፈታታቸው፣ የነዶክተር መረራ መፈታትና ኦነግ ናችሁ፣ ግንቦት ሰባት ናችሁ ቅብጥርሴ እየተባሉ ዘብጥያ የተወረወሩትን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መፈታታቸው ልቤን አርክቷል።
  2. ወያኔ ያሳደደቻቸውን ፓትርያርክ አሜርካ ደረስ በመሄድ ዶር ዐቢይ (በፍቅር ምክንያት “አንተ” ነው የምለው) እሱ በሚጓዝበት አውሮፕላን መልሶ አምጦቶ ወደመንበራቸው በመደመር፣ ወያኔ የከፋፈለችውን ሲኖዶስ አንድ የማድረጉ ጥረቱን፣ አደንቀዋለሁ። አበጀህ እለዋለህ! ወያኔ ልታቆመው አልቻለችም።
  3. ተቃዋሚዎቹን በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ አሳምኖ ከስደትም፣ ከበረሀም ስለመለሷቸው፣ የነዐቢይን ቡድን ድንቅ ሥራ እላቸዋለሁ። ታዲያ፣ በዚህ ላይ፣ ተቃዋሚዊች፣ ለነዐቢይ ሽክም እንዲያቃልሉላቸው እንጂ፣ ተጨማሪ ሸክም እንዳይሆኑባቸው እሰጋለሁ።
  4. የወያኔ አሽታሮች ያለበት ባንዲራ (ሆን ብዬ ነው ባንዲር ያልኩት – ነውምና (የፈለገ የሄን ያንብብ፡ http://wondimumekonnen.blogspot.com/2011/10/) ያልያዘ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የያዘን በሙሉ ወያኔ እያደነች የምታስረውን ሁሉ በማስቀረት፣ በዚያ ምክንያት ከወህኒ በወጡ በማግሥቱ የታሠሩትንም እነስክንድር፣ ደሳለኝንና ሌሎችን በመፍታት፣ ዛሬ፣ ኢትዮጵያው ውስጥ በኪሎሚትር የሚቆጠር ሰንደቅዓላማ አሰፍተው ኢትዮጵያውያን ሲሸከሙ ማየት ልዩ ደስታን ሰጥቶኛል። አሁንም የአንድነታችን፣ የጀግንነታችን፣ የልምላሜአችን ምልክት የሆነችው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቃችን ከፍ ብላ ትውለብለብ! ወደፊት ዐቢይ! ወደፊት! ግፋበት! ስለሰንደቅ ዓላማ ትንሽ ልበል። በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉት፣ አርማቸውን ያኑሩብት። ሕዝቡ ግን ሌጣውን ይያዝ።
  5. የኤርትራው ሰላም አስገራሚ ቢሆንም፣ ገና አላምጬው አልዋጥኩትምና አስተያየት ከመስጠት ለጊዜው ልቆጠብ። ግን እነ ዐቢይ እዚህ ላይ ማንም ደፍሮ ሊያደርገው የማይችለውን አድረግዋልና፣ እርማጃቸውን በአግራሞት አየዋለሁ።
  6. ዓቢይ ለኢትዮጵያ ያለውን ፈቅር ሲገልጽ ቆይቷል። የሚመርጣቸው ቃላት ልብ ሰርስረው የሚገቡ ናቸው። ተቺዎቹ ዓይናችንን ለማሳወር የሚጠቀም ታክቲክ ነው ይሉናል። ምን ሊጠቀም? ሺህ ጊዜ ልታወር። እኔ ወድጄዋለሁ። በዘመኑ አማርኛ ተመችቶኛል። በተለይ ጀርመን ላይ ያደረገው ንግግር ግን ከመቀመጫዬ ብድግ አድርጎኛል። እንዲህ ነበር ያለው።

“እርግጠኛ መሆን ያለባችሁ አንድ ነገር፡

ኢትዮጵያ ማንም ተነስቶ በወደደው ልክና መልክ እንድቂጣ ጠፍጥፎ የሚጋግራት የግል ረስት ሳትሆን፣ ዘመናትን ያስቆጠረች ታላቅ ሕዝብ የመሠረታት ታላቅሀገር መሆኗን ነው።

……..
ሀገሬ አንቀላፍታ ይሆናል እንጂ አልሞተችም!

ሀገሬ ድክማ ይሆናል እንጂ አልተሸነፈችም!

ሀገሬ ቀጥና ይሆናል እንጂ አልተበጠሰችም!

“አፌ ቁርጥ ይበልልህ” አሉ እማማ ብርዞ!!!!!

እንዲህ አገሬን የሚያሽሞነሙናትን ትቼ የሚያዋርዳት ተመለሶ እንዲመጣ መንገድ ልክፈትለት እንዴ? ዐቢይ እኮ፣ በቋንቋችን ስሊሚኮራ፣ ፈረንሳይ አገር፣ በአማርኛ ነበር የተናገረው። የትስ ቢሆን? ከዐቢይ የተሻለ በአሁኑ ጊዜ፣ በአሁኑ ሰዓት፣ በዛሪዪቱ ኢትዮጵያ ከየት ሊመጣ ነው? ሁሉንም በፍቅር ሰንሰለት ሊያስር እየሞከረ ነው። አንድ ነገር ግን፣ እላለሁ። ፍቅር ለማይገባቸው አንዳንዴም ፈርጠም ማለት ያስፈልገዋል። ዳዊትም ጎሊያድን በመግደል ነበር የጀመረው። ግደል ባልለውም፣ ፈቅር ያልገዛውን ሕግ እንዲገዛው ኮስተር ማለት ያስፈልጋል።

አዎን የለውጡ ቀልባሾች፣ አማራው ላይ በወልቃይትና በራያ አካባቢ የሚያደርጉትን፣ ኦሮሞው ላይ በሶማሌ እና በአሶሳ የሚያደርጉትን፣ ከየቦታው አማራው እንዲፈናቀል በሚያደርጉት ደባ፣ በአዲስ አበባ ባለፈው ሰሞን በተደረገው የጅምላ እስራትና በቡራዮ አካባቢ ባየነው ነገር ተስፋ ወደሚያስቆርጥ እየገፉን እንዳሉ እናውቃለን። ብዙ ሰዎች ተስፋ ቆርጠዋል። ዐቢይ ግን በሚቀጥሉት 10ተ ዐመታት ተስፋ ሰንቆልን፣ እነዚህን ደባ ሁሉ አስወግዶ ሰላም የሰፈነባት፣ ከድኅነት የተላቀቀች፣ መሰደድ የሚቀርላት፣ መታሰር መገደል የማይኖርባት፣ ፍትህ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ሊገነባልን ሲነሳ እኛንም ከጎኑ እንድንቆምና አንድ እንድንሆን ድምጹን ከፍ አድርጎ ይጠራናል። ዛሬ እነ ዐቢይን መቃወም ማለት እየወቁም ሆነ ባለማወቅ ለ27 ዓመታት ሙሉ ረግጠው ለገዙን ወያኔዎች እንደገና ተመልሰው ከበፊት በበለጠ በፊሮ ረግጠው እንዲገዙን መንገዱን ጠርገን በሩን ወለል አድረገን እንደመክፈት ነው። የናንተን እንጃ፣ እኔ ግን ከዚህ በኋላ ወያኔን የሚሸከም ጫንቃ የለኝም።

ዐቢይን የሚቃወሙም፣ ከወያኔ ውጭ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ምክኒያት አላቸው። ምክኒያታቸውም አሳማኝ ነው። ግን ዐቢይን በጥርጣሪ እንዲያዩት የሚያደርጉ፣ ከላይ የተገለጹት ድርጊቶችን የሚፈጽሙ እነማን እንደሆኑ አሻግሮ ማየት ይኖርባቸዋል። ዛሬ እነዚህ መሠርይ ኃይሎች አመራር፣ በአብዛኛው መቀሌ መሽገዋል። መቀሌ የወንጀለኞች መሸሸጋያ አይነኬ ሆናለች። ከዚያ ሁነው ወልቃይቴውችን ያርዳሉ። ማን ተናግሯቸው! የራያውን ደም የፈሳሉ። ማን ተው ብሏቸው! አፋርን ያሰቃዩታል። ማን ሊያቆማቸው ሞክሮ! ጸረ-ለወጦች ከኢትዮጵያ በዘረፉት ገንዘብ፣ ቦዘኔዎችን እየገዙ እዚህም እዚያም ኢትዮጵያ ውስጥ ደም ያፈሳሉ። 27 ዓመት ሙሉ የቀበሩት የዘር ፈንጂን፣ መቼ በስድስት ወር ልንገላገለው እንችላለን? ይኸ ሁሉ ወንጀል የሚያከተመው፣ መቀሌ የተሸሸጉት የሕውሀት ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር ሲውሉና ትግራይ ስትደመር ብቻ ነው። ያ ደግሞ ብልሀትና ጊዜ ይጠይቃል። የትግራይን ሕዝብ፣ ከወያኔ አዚም ወይም ምትሀት እንዲላቀቁ እንጸልይላቸው ልበል?

አንድ አስገራሚ የሀሳብ ልውውጥ በማኅበራዊ ሜዲያ አነበብኩ። እንዲህ ይላል፡

የኔ ጠበቃ፡

እሱ ከነሱ ጋር 27 ዓመት እንደነበር አንዘንጋ። ያውም የብሰሳ ድርጅትን የፈጠረው እሱ እንደነበር ባንዘነጋ መልካም ነው። ጥያቄው ካላችውትም ማላዘኑ ለምንአልሰራም ወይም ለምን ሁሉንም አላስተካከልም ሳይሆን፣ አማራው ሲገደል ሲፈናቀ ግፍ ሲፈፀምበት ለምን ዝም አለ። እናንተ የማታዩት ከሆነ ወይምየማሰሙ ከሆነ ወገኑ ለታረደበት ወገኑ ለተፈናቀለበት ተወልዶ ያደገበትን ቦታ ስፋት እየተበለ ለሚንገላታው ስድስት ወር አይደለም አንድ ደቂቃምይከብዳል። እስቲ በአማራው ላይ የምፈፀም ግፍ በኦሮሞ ላይ ቢደርስ ልዩነቱን ታዩት ነበር። ፍቅር የሚሰራው ለአማራው ብቻ ነው? በነገራችን ላይ አገሪቷንየሚያስተዳድረው አቢይ ሳይሆን አሁንም ወያኔ ነው።

ይኸ አባባል ዕውነትነት ያለው ይመስላል። የዚህ ዓርፍተ ነገር ደራሲ ግን፣ ይኸ ወንጀል አማራ ላይ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ብሔርሰብ ላይ፣ እየደረሰ መሆኑን ያለመገንዘቡ ትንሽ አሳስቦኛል። ቡራዩ የታረዱት አማሮች እኮ አይደሉም። ከሁለት ቀናት በፊት አሶሳ ውስጥ የተገደሉት፣ አንድ መንደር በሙሉ ቤታቸው የተቃጠለባቸው፣ በሕይወት የተረፉትናወደ ነቀምት የጎረፉት ኦሮሞዎች እኮ ናቸው። ሶማሌስ በአቅሟ ስንት አሥርተ ሺህ ኦሮሞዎችን አፈናቅላ የለ? ሁሉም ቦታ ጸረ ለውጥ ኃይሎች ደም እያፈሰሱ ነው። ዐቢይ ያ እያናደደው “በሉ እንግዲህ ይኸን ያፈሰሳችሁትን ደም ጠጡት!፡” ብሎ በምሬት እንደተናገረ አልሰማችሁም? ለማ አማሮች ሲፈናቀሉ ዝም አላለም። እርምጃም ወስዷል። የኽ ሲፈጸም ዝም ብለው ያዩትን የአደፓ ባለሥልጣናት እንዳሉ ጠራርጎ አባሯቸዋል። ጥሩ ለመሥራት እየጣሩ ነው። የ27 ዓመቱን የወያኔ ሰንኮፍ ግን ገና ነቅለው ለመጣል ብዙ ይቀራቸውል። ገና መቸ ነክተውት። ፈተና አለባቸው። በኔ እይታ በዚህ ሂደት ገና ብዙ ደም ሊፈስ ይችላልና እናስብበት። ለውጥ ያለ መራራ ትግልና መስዋዕትነት አይገኝም።

የአንድ የሌላ ብልህ ሰው መልስ እንዲህ ይነበባል፣

GG

አንዳንድ ጊዜ የኔ ጠበቃ ሃሳብ አይነት በኔም አእምሮ ይመላለሳል። እናም ዶ/ር አቢይ ያው ኢሓዴግ ነውና ሊምራን አይገባም ዛሬውኑ ስልጣን መልቀቅ አልበት የሚል ሃሳብ ብልጭ ይልብኛል ማለቴ ነው። ሆኖም የሚተካውንና ከሱ በተሻለ ህኔታ ከዛሬ ጅምሮ እከሌ ማስተዳደር ይሻል ነበር ብላችሁየምታስቡትን ሰው በመጠቆም ሃሳብ ብታካፍሉኝ።

ድንቅ መልስ ነው። እንዲህ ዓይነት አቀራረብ ብልህነት ነው። በዚህ አባባል፣ የኔ ጠበቃ የተባለውም ጸሐፊ እያቅማማ ችግሩ የኸ ነው ይላል። ቁጭቱ ግንከተቃዋሚዎቹ ማንንም ባለማዘጋጀታችን ነው ይላል።

ለማንኛውም ወደ ርዕሴ ልመለስ። ብደግፈው ባልደግፈው ዶር ዐቢይ መኖሬንም እንስክነአካቴው አያውቅም። ኢሚንት ነኛ! ቢሆንም መሀላዬን ልሰንዘር። እነ በግሌ እንዲህ እለዋለሁ።

ዶክተር ዐቢይ!

ባልደግፍህ እንኳን እንቃፋት ላልሆንብህ ቃል በምድር፣ ቃል በሰማይ እገባልሀለሁ!!!!!!

እግዞአብሔር ኢትዮጵያን ይባርካት!

Top picture: Ethiopia Prime Minster Dr Abiy Ahmed’s first speech in full

(Visited 723 times, 1 visits today)

You might be interested in